Monday, May 20, 2013

NEVIS Review No 17 , Section II , Ref# 17.2NEVIS Review No 17
Section II
Ref# 17.2
May 20, 2013
------------------------------
BOOK REVIEW of Hiwot Teferra’s book -TOWER IN THE SKY”
ኢህአፓ እና ያልተገለጠው ክህደት
Reviewe By Wosenseged Gebrekidan
(Credit- ሎሚ (Lomi) magazine)

የመፅሐፉ ርዕስ፡- TOWER IN THE SKY
የመፅሐፉ ደራሲ፡- ሕይወት ተፈራ
የመፅሐፉ ገፅ ብዛት፡- 437
የመፅሐፉ ዋጋ - 74 ብር
አሣታሚ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ
--------------------
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ይባላል፡፡ እውነት ነው፡፡ እኔ በዚህ አባባል ላይ ጥቂት ነገር ማከል ፈለግኩ፡፡ የጎደለን የታሪክ ክፍተት ምዕራፍ መሙላት ደግሞ የበለጠ ሙሉ ሰው ያደርጋል ማለት ወደድኩ፡፡ ይህንን እንድል ያደረገኝ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አማካኝነት ለህትመት የበቃው TOWER IN THE SKY የተሰኘው የዳጎሰ መፅሐፍ ነው፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተፅፎ ለህትመት የበቃው ይህ መፅሐፍ 1960ዎቹ መባቻ አንስቶ እስከ 1970 አጋማሽ ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ በተለይም ለውጥን በመሻት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸውን ወጣቶች ተጋድሎ፣ በተለይ በተለይ ደግሞ በዘመኑ ገናና ሥም የነበረውን የኢህአፓን እንቅስቃሴ በዓይነ ህሊና የሚያስቃኝ መራር ዕውነታን የያዘ መፅሐፍ ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፣ እስከዛሬ ያልተነገረውን፣ ያልተገለጠውን፣ ከአርባ ዓመት በላይ ተዳፍኖ የቆየውን በኢህአፓ ውስጥ የተፈጠረውን የዕርምት እንቅስቃሴ፣ የእንቅስቃሴውን መሪዎችና ነዳፊዎች እስከመጨረሻው በሚያምኗቸው በራሳቸው የትግል አጋሮች የተፈፀመባቸውን አሳዛኝ የክህደት ተግባር ወዘተ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፣ አስደናቂ ግን ደግሞ አሰቃቂና አስጨናቂ ታሪክ በውስጡ አምቆ ይዟል፡፡

ደራሲዋ ሕይወት ተፈራ ነች፡፡ ሕይወት ተፈራ በዚያ የለውጥ እንቅስቃሴ ወቅት በኢህአፓ ውስጥሳታውቀውቁልፍ የአመራር አባላቶች መሀከል አንዷ ለመሆን የበቃች ነበረች፡፡ ሳያውቁ አመራር መሆን ምን ማለት ነው? ምላሹን ከመፅሐፉ ታገኙታለችሁ፡፡ ደራሲዋ እንዲህ ያሉ በርካታ አስገራሚና አስጨናቂ ክስተቶችን እየተረከች ትናንትናን በዛሬ መነፅር እንድናይ በሚያስችል መልኩ ለአንባቢያን ታላቅ የታሪክ ሰነድ እነሆ ብላናለች፡፡ ሕይወት፤ ያንንተከድኖ ይብሰልየተባለ ታሪክ፣ ያንን ብዙዎች ሊያነሱት እንኳ የማይደፍሩትን መራር ዕውነት፣ ቀለል ባለ የአተራረክ ስልት፣ ምስል ከሳች በሆነ ፍሰት፡- ይዛን ለዘመናት የኋሊት ትነጉለች፡፡ እናም የታሪካችንን ሌላ ጎን ጥርት አድርጋ ታሳየናለች፡፡ እንደው በአጭሩ ሕይወት ወደ ሌላኛው የታሪክ ህይወት ባሕር ውስጥ ትዘፍቀናለች፡፡ እናም በሐዘኗ ታሳዝነናለች፡፡ በሥቃይ ታስቃትተናለች፡፡ በትግሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ታፍገመገምናለች፡፡ በሞትና በህይወት መሃል ታንጠራውዘናለች፡፡ በእፎይታዋእፎይታሰኘናለች፡፡ ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም፡፡
ሕይወት ያኔ ወደ ትግሉ ስትገባ ገና 18 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡ በዚያ የአፍላነት ዕድሜዋ በማትረሳው አጋጣሚ በፍቅር ተለከፈች፡፡ ያፈቀረችው ወጣት በሕዝባዊ ፍቅር የተነደፈ ነበረ፡፡ እሷንም በሕዝባዊ ለውጥ ፍቅር ነደፋት፡፡ በዚያው የለየላት ለውጥ ናፋቂ ወጣት፡፡እሣት! እሣተ መለኮትእንዲሏት አይነት ታጋይ ወጣት፡፡ (ወደትግል የገባችበትን ሁኔታ በመፅሐፏ የተረከችበት እጅግ ዘለግ ያለ ታሪክ እጅጉን ሲያጥር እንዲህ ነው የሚሆነው) ከዚያስ?....ከዚያማ ህይወትን እስከመስጠት ድረስ የሚያዘልቅ ተልዕኮ ስትፈፅም፣ በአጋጣሚ ከተጠመደባት ወጥመድ አፈትልካ ስትወጣ፣ ከሞት ጋር ፊት ለፊት ስትፋጠጥ፣ በዕድልና በተዓምር ሞትን ጥላ ስታልፍወዘተ አንድ በአንድ ትተርክልናለች፡፡ ስሜትን ሰቅዞ፣ ትንፋሽን አሳጥሮ፣ ልብን የሚያኮማትረው ትረካዋ እስከመጨረሻው ገፅ ድረስ ይቀጥላል፡፡

ደራሲዋ ለለውጥ የተነሳሳ ትውልድ፣ በወጣትነት የተስፋ ዘመኑ የሃገርንና የሕዝብን መፃዒ ዕጣ-ፈንታ የሰነቀ ትውልድ፣ ታላቅ ራዕዩን፣ ምኞቱን፣ ህልሙን፣ ለሌሎች የተሻለ ሕይወት የራሱን ህይወት አሳልፎ መስጠቱን፣ በራሱ መሪዎች የተፈፀመበትን ክህደት፣ በትግሉ ውስጥ ያልተጠበቁ አሳዛኝ የሆኑ ክስተቶችን እናተዓምራቶችን”… ወዘተ እንደልቃቂት በሚተረተር አንዳች ኃይል ባለው ትረካ ትነግረናለች፡፡ መፅሐፉ፤ በዚያ መራር የትግል ዘመን ውስጥ ያለፉ፣ አሁንም በህይወት ያሉ የዚያ ትውልድ አባላት ትናንትናን በትዝታ የሚያዩበት፣ እንዲሁም ሁሉ ያንን ሁሉ መስዋዕትነት በጠየቀ ትግል ውስጥ የመሪዎቻቸው ሚና እና ምስጢራዊነት እስከምን ድረስ ጠሊቅ እንደነበር የሚያስተውሉበት፣የትውልዳቸው የንሰሃ መዝሙር ነውብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡
TOWER IN THE SKY “የበላይ አካላትአመራሩበሚሉ ጥቅል ስያሜ በአባላቱ የሚጠራው የኢህአፓ አመራር የፈፀመውን ስህተት እና የዚያ ትውልድ ትግል ጨንግፎ የቀረበትን ምክንያትወዘተ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚያ ትግል ውስጥ ያለፉና በህይወት ለመኖር የታደሉ የድርጅቱ አባላቶች በወጉ ሊነኩት ያልደፈሩት እና ብዙዎችም ሊደፍሩት በማይሹትምስጢራዊነትየተነሳ ተድበስብሶ ዘመናትን የዘለቀው ታሪክ ነው በደራሲዋ ሕይወት ተፈራ ብዕር የተገለጠው፡፡
እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም ክፍሉ ታደሰ፣ አስማማው ኃይሉ (አያ ሻረው) በእንግሊዘኛ ቋንቋዶንኪስ ሆምየተሰኘውን መፅሐፍ የፃፈው ወሎዬው ይማም መሐመድ .. ከኢህአፓ ድንቅ ተጋድሎ በስተጀርባ ያለውንና በምስጢራዊነት ሽፋን የተጀቦነውን የድርጅቱን ድክመት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ሕይወት ተፈራም TOWER IN THE SKY የሚል ርዕስ በሰጠችው መፅሐፏ የጎደለውን ያንን የታሪክ ምዕራፍ መሙላት የሚያስችል ታላቅ ሥራ ነው ያበረከተችልን ፡፡ በተለይም የአመራሩን ክህደት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የዘመን መስታወት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሕይወት ተፈራ፤ ከሐረር እስከ አደስ አበባ ያሳለፈችውን የህይወት ሰንክሳሮች፣ ሻይ የጠጣችባቸውን ካፌዎች፣ የኖረችባቸውን የአ/አበባ መንደሮችን፣ 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ አምስተኛ በር በኩል የሚገኘውን አፍንጮ በር እና አካባቢውን፣ ፒያሳን፣ መርካቶን፣ አራት ኪሎንወዘተ በዚያ ጊዜ የነበራቸውን ገፅታ በምልሰት ታስቃኘናለች፡፡
በመፅሐፉ ውስጥ የእኔን ስሜት እጅጉን የነካው፣ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደግሜ ደጋግሜእንዲህ ያለ ክህደት እንዴት ይፈፀማል?” ብዬ እንድጠይቅ ያስገደዱኝ ታሪኮች ታጭቀውበታል፡፡ እዚህ ላይ ጥቂት ክፍል ታሪክ ለአብነት ያህል መቀንጨብ ወደድኩ፡፡ ደራሲዋ ከፍቅሬ ዘርጋው ጋር ወደ መቀሌ ስታቀና እንዳየሱስ በተባለ ቦታ በሚገኝ የፍተሻ ኬላ ላይ የገጠማትን ሁኔታ ላስቀድም፡፡ እነሆ፡-
“…ፍቅሬ ዘርጋው ከደሴ ወደ መቀሌ የሚወስደውን አውቶብስ ስንሳፈር ዘና ብሎ ነበር፡፡ እንዳየሱስ ፍተሻ ኬላ ላይ የሚደረገው ፍተሻ ጠንካራ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ አውቶብሱ ፍተሻው ኬላ ሲደርስ ቆመ፡፡ ወንዶች ተሻፋሪዎች ለፍተሻ ሲወርዱ፣ ፍቅሬ ዘርጋው ቢጫ እና አረንጓዴ ሻንጣዎቹ የተቆለፉበትን ቁልፍ ሰጥቶኝ ወረደ፡፡ ሁለት ወታደሮች አውቶብስ ውስጥ የቀረነውን ሴት ተሳፋሪዎችን እቃ መፈተሽ ጀመሩ፡፡
“…ፍቅሬ ዘርጋው ከአውቶብሱ ከወረዱት ተሳፋሪዎች ቆሟል፡፡ ገፅታው ላይ ጭንቀት ይነበብበታል፡፡ ወደ አውቶብሱ ውስጥ በተጨነቀ መንፈስ እያየ ግንባሩን ያወረዛውን ላብ በያዘው መሃረብ ቶሎ ቶሎ ይጠርጋል፡፡ ለምን እንደሆነ ባይገባኝም፣ መጨነቁ ታወቀኝ፡፡ፈታሾቹ ወታደሮች እየፈተሹ እኔ ወዳለሁበት ቦታ ደረሱ፡፡
ረዘም ያለው ወታደር ወደ ሻንጣው እየጠቆመይኼ ሻንጣ የማነው?› ሲል ጠየቀኝ፡፡
የእኔ ነውአልኩት፡፡
አብሮት ያለው ጓደኛውንአውርደውሲል አዘዘው፡፡ ሌላኛው ወታደር እንደታዘዘው ሻንጣውን አውርዶ ባዶው ወንበር ላይ አስቀመጠው፡፡ ረዥሙ ወታደርክፈቺውአለኝ፡፡ ከፈትኩት፡፡ በውስጡ ልብሶች ይኖራሉ ብዬ ነበር የገመትኩት፡፡ በሻንጣው ውስጥ ያለው የወታደር ደንብ ልብስ ነበር፡፡
ረዥሙ ወታደርእነዚህ ምንድናቸው?› ሲል ጠየቀኝ፡፡
የባለቤቴ ደንብ ልብስ ነውአልኩት፡፡
ባለቤትሽ የጦሩ አባል ነው?›
አዎን - ወታደር ነው፡፡
እሺ መልሺውአለኝና ሌላኛውን ቢጫውን ቫንጣ እየጠቁመ የማን ሻንጣ እንደሆነ ጠየቀ፡፡ እንደመሳቅ እያልኩኝ አልኩት፡፡ በዚህ ሁኔታዎች አደገኛ እንደሚሆኑ እየገመትክ ነበር የደመነፍስ መልስ የሰጠሁት፡፡
እሺ ተወውብሎ አልፎኝ ወደሚቀጥሉት ተፈታሾች ተሻገረ፡፡….” (ገፅ 254- 255)
አንባቢ እዚህ ላይ ሲደርስ በርካታ ጠያቄ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ለምን? በዚያ አስጨናቂ ዘመን፣ በዚያ ወጣቶች ሁሉ እንደአውሬ በሚታደኑበት፣ በዚያ ዜጎች በቶርቸር በሚተለተሉት ዘመን፣ እንኳንስ ስርዓቱን የሚቃወሙ ነፍስ የማያውቁ ህፃናት የኢህአፓን በራሪ ወረቀት ይዛችኋል ተብለው በአደባባይ በሚረሸኑበት ዘመንወዘተ ለፍትህና ለነፃነት እንታገላለን የሚሉ የፓርቲው አመራሮች፣ የሚያምኗቸውን ጓደኞቻቸውን አሳልፈው ለሞት እንዴት ይሰጣሉ?...እነሱ ቆመው ሲገደሉ ለማየት ሞራል ያመጡት ከየት ነው? …ሕይወት አቦ ሰጥምላሽ የወታደሩን ጥያቄ ባታልፈው ኖሮ የሚከሰተው ምንድነው? ወታደሮቹ በቸልተኝነት አለፏት እንጂ ሁለተኛውን ሻንጣ ቢፈትሹትስ? በውስጡ ምን ይገኝ ነበር? ከዚያስ ምን ይከተላል? እነዚህና እነዚህን መሰል ጥያቄዎች እንኳንስ በዚያ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝን፣ የአንባቢን ልብ የሚያኮማትሩ ናቸው፡፡ ሕይወትም በዚያ ቅፅበት እነዚህን ጥያቄዎች ራሷን በራሷ ጠይቃለች፡፡ እናምየሆነ ክህደት እየተፈፀመብኝ እንደሆነ ተሰማኝስትል የተሰማትን ስሜት ትገልፀዋለች፡፡
“….ወንዶቹ መንገደኞች ተፈትሸው መታወቂያቸውን እያሳዩ ተመልሰው ወደ አውቶብስ ገቡ፡፡ ፍቅሬ ዘርጋው መጥቶ አጠገቤ ተቀመጠ፡፡ የሆነ የእፎይታ ስሜት ቢነበብበትም፣ ድንጋጤና ጭንቀቱ ያስከተለው ላብ በጉንጩ ላይ ይወርድ ነበር፡፡ በዚያው ስሜት ውስጥ ሆኖ በለሆሳስ ድምፀትአመሰግናለሁአለኝ፡፡… ” ስትል ትረካዋን ትቀጥላለች፡፡
ሕይወት መቀሌ ከደረሱ በኋላ፣ ስለሻንጣዎቹ እና በውስጡ ስለያዙት ዕቃዎች ምንነት፣ ለምንስ የያዙት ነገር እንዳልተነገራት ጠየቀችው፡፡ ፍቅሬ ዘርጋው እየሳቀ የሚከተለውን ምላሽ ሰጣት፡-
ጉዞ ከመጀመራችን በፊት በጉዳዩ ላይ ከጓዶች ጋር ተነጋግሬበት ነበር፡፡ በሻንጣዎቹ ውስጥ ያሉት ነገሮች ቢነገርሽ ልትረበሺ ትችያለሽ ተብሎ ነው ያልነተገረሽ፡፡ በሻንጣዎቹ ውስጥ ለተዋጊዎቻችን የሚሆኑ ወታደራዊ ዩኒፎርሞች፣ 12ሺህ ብር፣ የተለያዩ አብዮታዊ መዝሙሮች የተቀረፁባቸው ካሴቶች እና ሌሎች ዕቃዎች ናቸው የሚገኙት፡፡” (ገፅ 256)
ሕይወት፣ የፍቅሬ ዘርጋውን መልስራሴን አሳመመኝ፤ ግን ደግሞ ሳቅኩኝስትል ትገልፀዋለች፡፡ ለዚህ ምጥን ዳሰሳ ፅሁፍ አቅራቢ ግን የተሰማው ሥሜት በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ ታሪኩን ማንበቡ ብቻ አንቀጥቅጦኛል፡፡ ሕይወት ደግሞ የዚህ ስሜት የእጥፍ እጥፍ እንደሚሰማት መፅሐፉን ያነበበ ይረዳል፡፡ የተሰው እጅግ ብዙ ጓደኞቿ ተራ በተራ በዓይኗ ስር ድቅን ማለታቸው አይቀርም፡፡ እንደ ስመኝ ያሉ ትንታግ ወጣቶች፡፡ ስመኝ 22 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡ ሳቂታ፡፡ ሳቋ ቤት የሚያደምቅ፣ የማይጠገብ ፍልቅልቅ ወጣት ነበረች፡፡ ከአራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ መኝታ ክፍሏ ተሰናብታት የወጣችውነገ እንገናኛለንብላት ነበር፡፡ ያን ቀን እንደወጣች ቀረች፡፡ አልተመለሰችም፡፡ በርሳዋ ውስጥ በተገኘ ዲሞክራሲያ ዕትም ምክንያት ተገደለች፡፡ ምናልባትም ሕይወት፣ ፍቅሬ ዘርጋው የሰጣት መልስ ያንን የማይረሳው የስመኝን ሳቅ በህሊናዋ ውስጥ ሳያቃጭልባት አይቀርም፡፡
TOWER IN THE SKY አያሌ የዘመኑን ትውስታ ያቋድሰናል፡፡ ያኔ ድርጅቱ /አበባን አራት ቦታ ክፍሎ ነበር የሚንቀሳቀሰው፡፡ ዳዊት፡- ዞን አንድ (መርካቶ፣ ጉለሌ፣ ተክለኃይማኖትና አካባቢውን) ሲራክ፡- ዞን ሁለት (ንፋስ ስልክ፣ ቄራን እና አካባቢውን) ሕይወት፡- ዞን ሶስት (ካዛንቺስ፣ ቦሌን እና አካባቢውን) ሳሙኤል፡- ዞን አራት (አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ እንጦጦ እና አካባቢውን) በመምራት፣ ኮሚቴ በመመስረት፣ የአባላት ምስረታ በማካሄድ ፓርቲውን ለማጠናከር የሚያደርጉት ትግል ያወሳል፡፡ ደራሲዋ ሕይወት ተፈራ በነዚያ ዞኖች ውስጥ ተካታው በመታገላቸው ምክንያት በደርግ ወታደሮች የተገደሉ፣ ለእስር የተዳረጉ እና አሁንም በዓለም ዙሪያ የተበተኑ ታጋዮችን ተጋድሎ በምልሰት የተረከችበት ስልት አንባቢን በመቆጨት ስሜት ይንጣል፡፡
እነ ጌታቸው ማሩ፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ አገሬ ምህረቱ፣ አብዩ አርሴም፣ ስመኝ ለማ፣ መኮንን ባይሳ፣ ጣይቱ አሰፋ፣ ዮሐንስ ብርሃኑ፣ መላኩ ማርቆስ፣ እና ሌሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ የዚያ ትውልድ አባላት ውጣ ውረድና መስዋዕትነት እስካሁን ድረስ የሚፈለገው ውጤት ላይ ያለመድረሱ ሰበብ ምንድነው ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅና ነገሮችን እንድንመረምር ግድ ይላል፡፡ ሊመረመርም የሚገባ ነው፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፤ ሕይወት ተፈራ ባሳለፈችው የሥቃይና የመከራ ህይወት ውስጥ፣ እንደጠባቂ መልአክ ከሞትና ከሚሰቃየው ቶርቸር ምርመራዎች እንድትድን ያደረጓት ባለታሪኮች ከዚያኛው ጎራ ሆነው የፈፀሟቸው ተግባራቶች በእርግጥ ሆን ተብለውና ታስቦባቸው የተደረጉ ናቸው ወይስ በደመነፍስ የተደረጉ ናቸው? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡- መፅሐፉ፡፡

TOWER IN THE SKY ጌታቸው ማሩ እስከመጨረሻዋ የእስትንፋሱ ሕቅታ ድረስ ሲያምናቸው በነበሩ የትግል ጓዶቹ የተፈፀመበትን ዘግናኝ የግድያ ታሪክ፣ እንደ አዲስ እንድናውቅም ያደረገ ነው፡፡ መፅሐፉ በእርግጥ በዚያ ትውልድ ውስጥ የሚታየው መሰሪነት እና ያለመተማመን፣ ድመት ልጆቿን እንደምትበላ ሁሉ እስካሁን ድረስየእርግማን ነው እንዴ?” እንድንል ያደርገናል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የታሪክ አንጓ ሊመረመርና ልንወያይበት የሚገባያልተወለደ እውነትመሆኑን ነው የሕይወት መፅሐፍ በአፅንኦት የሚነግረን፡፡ ስለዚህም ነው መፅሐፉ፣ ሊነበብ የሚገባው ድንቅ መፅሐፍ ነው የምንለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ደራሲዋ የታሪክን ምዕራፍ ለመሙላት እና ታሪክን ለማጥራት ዛሬም የፈፀመችውን ህያው ተግባር ልናደንቅ ይገባል፡፡ እንደገና በዚሁ አጋጣሚ ይህ የተዳፈና ታሪክ ከዘመናት በኋላ ተፈልቅቆ ሲወጣ፣ ብዙሃኑ ኢንባቢ ታሪኩን በወጉ ያጣጥም ዘንድ ወደአማርኛ ቋንቋ ቢመለስ መልካም መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እንወዳለን፡
------------------------------------

( Ed’s note: The book review first appeared on an Amharic magazine, ሎሚ( Lomi )magazine, Volume 2. No 52, Miazia 2005 EC. We thank Wosenseged  for letting us reproduce it in NEVIS Review)
--------------------------------------------------------//---------------------------------------------------------